ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር ታላቁ የሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል። 

"ኢትዮጵያ እየመከረች ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ባለው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

በአሁኑ ወቅትም የውድድሩ ተሳታፊዎች ከሩጫው አስቀድሞ በተዘጋጀው የጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዋናው ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሕዝብ ወኪሎችም ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው። 

በዚህ ዋና የምክክር ጉባኤ ላይ፡ 

• የሀገር ግንባታ፣ 

• የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ 

• የፖለቲካ ሥርዓት፣ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ 

• የፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ጉዳይ፣ 

• የሃይማኖት ጉዳዮች፣ 

• የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ 

• ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች (የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳይን ጨምሮ)፣ 

• እንዲሁም ሙስና፣ መልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታን ያካተቱ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የሕዝብ ወኪሎች የሚመክሩባቸው ይሆናል። 

በመስቀል አደባባይ በተሰናዳው በዚህ የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መርሃ ግብር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራው አንደሞ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዲሁም የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም