አርጀንቲና ስዊዘርላንድን በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
አርጀንቲና ስዊዘርላንድን በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር አርጀንቲና ስዊዘርላንድን 3 ለ 1 አሸንፋለች።
ማለዳ ላይ በተጠናቀቀው እና በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አሌክሲስ ማካሊስተር በ10ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል አርጀንቲናን መሪ አድርጓል።
የ39 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ ለግቧ መቆጠር ምክንያት ሆኗል።
ሊዮኔል ሜሲ በዓለም ዋንጫ ታሪክ 10 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ የመጀመሪያ ተጫዋች ሆኗል።
ዳን ንዶይ በ67ኛው ደቂቃ የስዊዘርላንድን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ንዶይ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ጎሉን አስቆጥሯል።
የ27 ዓመቱ የስዊዘርላንድ አጥቂ ብሬል ኢምቦሎ በ72ኛው ደቂቃ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ኢምቦሎ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የተመለከተው በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቫር) ታይቶ አታሎ ወድቋል በሚል በተላለፈ ውሳኔ ምክንያት ነው።
ቢጫውን መጀመሪያ ያየው የአርጀንቲናው ሊያንድሮ ፓሬዴስ ሲሆን ውሳኔው ተሰርዞ ኢምቦሎ በቀይ ካርድ እንዲወጣ ተደርጓል።
ኢምቦሎ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
በፊፋ አዲሱ ሕግ አንድ ተጫዋች ቢጫ ካርድ ያለበት ተጫዋች ካታለለ ቀይ ካርድ እንደሚመለከት ይደነግጋል።
ውሳኔው ስዊዘርላንዶችን አላስደስተም።
ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በማለቁ ምክንያት 30 ደቂቃ ተጨምሯል።
ሁሊያን አልቫሬዝ 112ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ባስቆጠረው ጎል አርጀንቲና መሪ ሆናለች።
ተቀይሮ የገባው ላውታሮ ማርቲኔዝ በ121ኛው ደቂቃ የአርጀንቲናን አሸናፊነት ያረጋገጠችውን ጎል አስቆጥሯል። በውድድሩ ላይ ሁለተኛ ግቡን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
አልቫሬዝ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ከቀይ ካርዱ በኋላ በጥልቀት በመከላከል ጨዋታውን ወደ መለያ ምት የመውሰድ እቅድ የነበራት ስዊዘርላንድ ውጥኗ አልተሳካም።
ለሜሲ የዛሬ መርሐ ግብር በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ግብ ያላስቆጠረበት የመጀመሪያ ጨዋታ ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን አርጀንቲና ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።
በዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ አምስተኛ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው አርጀንቲና ለፍጻሜ ለማለፍ ከእንግሊዝ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ስዊዘርላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ ውጥኗ ሳይሳካ ቀርቷል።
ጨዋታውን ተከትሎ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሐምሌ 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳሉ።
ፈረንሳይ ከስፔን፣ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ለፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማሉ።