ቀጥታ፡

እንግሊዝ ኖርዌይን በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝ ኖርዌይን 2 ለ 1 አሸንፋለች።

ከእኩለ ሌሊት በኋላ በሚያሚ በተደረገው ጨዋታ አንድሪያስ ሼልድሩፕ በ36ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ኖርዌይን መሪ አድርጓል።

ጁድ ቤሊንግሃም በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ የእንግሊዝን የአቻነት ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ቶርብዮን ሄገም በ56ኛው ደቂቃ ኖርዌይን መሪ ቢያደርግም በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቫር) ታይቶ አርሊንግ ሃላንድ የማዕዘን ምት ከመመታቱ በፊት ኤሊዮት ሄንደርሰን ላይ በሰራው ጥፋት ጎሉ ተሽሯል።

ጨዋታው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ምክንያት ወደ 30 ደቂቃ አምርቷል።

ጁድ ቤሊንግሃም በ93ኛው ደቂቃ ለእንግሊዝ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

የኖርዌይ ግብ ጠባቂ ኦርጃን ኒላንድ ስህተት ለግቧ መቆጠር ከፍተኛ ድርሻ ወስዷል።

በጨዋታው ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው  የ23 ዓመቱ ቤሊንግሃም በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከመረብ ላይ ጎሎች ብዛት ስድስት አድርሷል።

ቤሊንግሃም ከቡድን አጋሩ ሃሪ ኬን ጋር በተመሳሳይ ስድስት ጎሎችን በዓለም ዋንጫው አስቆጥሯል።

በጨዋታው እንግሊዝ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ብትወስድም ኖርዌይ ግልጽ የግብ እድሎች በመፍጠር የተሻለች ነበረች።

ኖርዌይ በሁለተኛው  አጋማሽ የወሰደችውን ብልጫ ወደ ግብ መቀየር አልቻለችም።

ውጤቱን ተከትሎ እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች። አራት ውስጥ ስትገባ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

ለፍጻሜ ለማለፍ ከአርጀንቲና ስዊዘርላንድ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

የሰሜን አውሮፓዋ ኖርዌይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ የማለፍ ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።

ኖርዌይ በዓለም ዋንጫው ላይ የነበራት መልካም ግስጋሴ ሩብ ፍጻሜው ላይ ተገቷል።

ሰባት ጎሎቹን ያስቆጠረው የኖርዌው አርሊንግ ሃላንድ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩ ውጪ ሆኗል።

ከሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፊት በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ለደቡብ አፍሪካ የተጫወተው እና ዛሬ ህይወቱ ያለፈው የ25 ዓመቱ ጄይደን አዳምስ የሕሊና ፀሎት ተደርጓል።

ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም