ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞሪሺየስ የጀመረው አዲስ ቀጥታ በረራ ለንግድ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት አዳዲስ ዕድሎችን ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞሪሺየስ የጀመረው አዲስ ቀጥታ በረራ ለንግድ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞሪሺየስ ዋና ከተማ ፖርት ሉዊስ የቀጥታ በረራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞሪሺየስ የጀመረው አዲስ ቀጥታ በረራ የአፍሪካን ተደራሽነት በማስፋት የትስስር ጥረቱን የሚያጠናክር ስኬታማ ምዕራፍ ነው ተብሏል፡፡

የበረራው ማስጀመሪያ የመርሐግብር ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ በኢትዮጵያ የሞሪሺየስ ሪፐብሊክ አምባሳደር ኢንድራርጂት ባምቦዋ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሐግብሩ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ እንዳሉት፣ አዲሱ የበረራ አገልግሎት የሁለቱ ሀገራት የአፍሪካ ውህደትን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ይህ ድልድይ ለቀጠናዊ ትስስር፣ ለንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ለባሕል ልውውጥ አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በሞሪሺየስ እና በአዲስ አበባ በኩል ወደ ቀሪው ዓለም የሚደረገውን ጉዞ በማቀላጠፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ አዲሱ መስመር አየር መንገዱ በአፍሪካ ያለውን ትስስር ለማሳደግ ያለውን ስትራቴጂያዊ እቅድ ያሳያል ብለዋል።

ሞሪሺየስ የአየር መንገዱ 41ኛዋ የአፍሪካ መዳረሻ መሆኗን የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ይህ በረራ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ዓላማዎችን በመደገፍ የኢኮኖሚ ትብብርን እንደሚያሻሽል አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሞሪሺየስ አምባሳደር ኢንደራርጂት ባምቡዋ፣ ይህ የበረራ መጀመር በሁለትዮሽ ግንኙነት ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን የአፍሪካ ልቀት፣ ጽናትና ፈጠራ ምልክት ሲሉ ያደነቁ ሲሆን፣ አዲሱ መስመር በአፍሪካ እና በሕንድ ውቅያኖስ ቀጠና መካከል ያለውን ትስስር በእጅጉ እንደሚያሳድግም እምነታቸውን ገልጸዋል።

ይህ አዲስ የበረራ አገልግሎት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያገናኝበትን መረብ ይበልጥ ያጠናክራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም