ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል የአሰራርና የቴክኖሎጂ አቅም ገንብታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል የአሰራርና የቴክኖሎጂ አቅም ገንብታለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል የህግ፣ የአሰራርና የቴክኖሎጂ አቅም መገንባቷን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለፀ።
ከትናንት ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃ ደኅንነት ፎረም ተጠናቋል።
በመድረኩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ የሳይበር ደኅንነት፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና መሰል ዓለም አቀፍ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ በስፋት ምክክር ተደርጎበታል።
በዚህ ወቅት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ እንዳሉት፤ የሳይበር ደህንነት ስጋቶች ድንበር የለሽ በመሆናቸው ስጋቶችን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ህጎችን የማጣጣምና የቅንጅት ስራ ወሳኝ ነው።
ሃገራት የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅና የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከላከል ተናባቢ ህጎች ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተው፣ ኢትዮጵያም በዚህ አግባብ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል የህግ፣ አሰራርና ቴክኖሎጂ አቅምን ገንብታለች ብለዋል።
ፎረሙ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ለማዘጋጀት ያላትን አቅም ለማሳየትና ለገጽታ ግንባታ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑንም ተናግረዋል።
የናይጄሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፎረሙ አባል አግበዲ ዬቲዬኔ ፍሬድሪክ (ዶ/ር) ፤ በኢትዮጵያ በተዘጋጀው ፎረም መሳተፋቸው ከተለያዩ ሀገራት ልምድ ለመለዋወጥ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በህንድ በሚገኘው የካሊንጋ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ቫሩን ሱትራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ፎረሙን ሙያዊ በሆነ አግባብ መምራቷ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።