ቀጥታ፡

የአፍሪካ የትምህርት ኢኖቬሽን ኤክስፖ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ) 2026ቱን የአፍሪካ የትምህርት ኢኖቬሽን ኤክስፖ በመጪው ሐምሌ 6 እና 7 ቀን 2018 . በአዲስ አበባ ይካሄዳል

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ያዘጋጀው ይህ ኤክስፖ፤በትምህርት ዘርፍ የዲጂታል ሽግግርን ማፋጠንና ለአፍሪካ የክህሎት ዘመን የአዳዲስ መፍትሔዎችን ተደራሽነት ማስፋትበሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ታውቋል።

ይህ አህጉራዊ ኤክስፖ በአፍሪካ የትምህርትና ክህሎት ሥርዓት ውስጥ ያሉ የጥራት፣ የተደራሽነትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ክፍተቶችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት ለመፍታት ያለመ ነው።

መድረኩ በተለይም አዳዲስ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎችን በማስተዋወቅ የአፍሪካን የትምህርት ዘርፍ ማዘመን በሚቻልባቸው ስትራቴጂዎች ላይ ይመክራል።


 

በኤክስፖው በትምህርት፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በሮቦቲክስ ዘርፎች ከፍተኛ ተፅዕኖ ማምጣት የቻሉ 20 በላይ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ለዕይታ ይቀርባሉ።

በተጨማሪም በዲጂታል ትምህርት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በአረንጓዴ ክህሎቶች፣ በምርምርና በኢንዱስትሪ አጋርነት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ውይይቶቹም ከአህጉራዊ የትምህርትና የሳይንስ ስትራቴጂዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው ተገልጿል።

በኤክስፖው 300 በላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ የፈጠራ ባለቤቶች፣ ተመራማሪዎች፣ የልማት አጋሮች እና የቴክኖሎጂ መሪዎች በአካል እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ታዳሚዎችም በበይነ መረብ አማካኝነት በሁነቱ ላይ እንደሚሳተፉ ኢዜአ ከአፍሪካ ኅብረት ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ኤክስፖው በአጠቃላይ በአፍሪካ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የዲጂታልና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።

ይህም አፍሪካ ለቀጣይ የኢኮኖሚ ሽግግር ብቁና ዝግጁ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንዲሁም የአህጉሪቱን የሰው ኃይል አቅም ለማጠናከር ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርላት ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም