ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የተገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ለትራፊክ ፍሰቱ መሳለጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶችና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለትራፊክ ፍሰቱ መሳለጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በማዘመን እና ዘመናዊ የመንገድ መሰረተ-ልማቶችን በመዘርጋት፣ የትራፊክ ፍሰትን ከማቀላጠፍ ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ አካባቢን መፍጠር አስችሏል፡፡

ሰፊና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ መንገዶች በመገንባታቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከማረጋገጡም በላይ፣ የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነት በማስጠበቅ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

አስተያየታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች በከተማዋ የተሰሩት አዳዲስ መንገዶች እና የኮሪደር ልማት ስራዎች የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ አዎንታዊ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል። 


 

አሽከርካሪ የሆኑት ኃይሌ ዘመድኩን እና ጤናዬ ጠንክር እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ ለትራፊክ ፍሰት አመቺ እና ዘመናዊ መንገዶችን በመፍጠር ስጋት የለሽ የማሽከርከር ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየሩት እነዚህ ውብና ሰፋፊ መንገዶች፣ የዲዛይን ጥራታቸውና የተሟላ የመንገድ ምልክቶቻቸው ለትራፊክ አደጋ መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።


 

የኮሪደር ልማት ለከተማዋ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ለአሽከርካሪዎች የላቀ የደህንነት ስሜትና የጉዞ ቅልጥፍናን የሰጠ ስኬታማ የልማት ስራ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

አሽከርካሪ ብሩክ ግሩም፤ የኮሪደር ልማቱ የነበረውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመቅረፍ ተሽከርካሪዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረጉ ጉዞን በአጭርና በአስተማማኝ ሁኔታ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።


 

የመንገድ አቅም መጨመሩ ለትራፊክ ፍሰቱ መሻሻል ብቻ ሳይሆን፣ አደጋዎችን በእጅጉ በመቀነስ ለአሽከርካሪዎች ትልቅ የደህንነት እፎይታን የፈጠረ ውጤታማ የልማት ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ዘርጋ እንደገለጹት፤ የተከናወኑት የኮሪደር ልማት ስራዎች የትራፊክ ፍሰቱን በማቀላጠፍና የከተማዋን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሰላማዊ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።


 

ይህ ዘመናዊ የመንገድ አውታር እግረኞች በደህንነት ተጠብቀው በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ፣ በያዝነው በጀት ዓመት በሰውና በንብረት ላይ ይደርስ የነበረውን የመንገድ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የመንገድ ደህንነትን በማረጋገጥና የትራፊክ መጨናነቅን በማስወገድ፣ በከተማዋ ለሚደረግ ማንኛውም አይነት የጉዞ እንቅስቃሴ አስተማማኝና ቀልጣፋ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም