በዞኑ የተገኘው ሰላም የግብርና ስራችንን በተረጋጋና በተደራጀ መልኩ ለማከናወን አስችሎናል - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የተገኘው ሰላም የግብርና ስራችንን በተረጋጋና በተደራጀ መልኩ ለማከናወን አስችሎናል - አርሶ አደሮች
ገንዳውኃ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የተገኘው ሰላም የግብርና ስራቸውን በተረጋጋና በተደራጀ መልኩ ማከናወን እንዳስቻላቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ።
አርሶ አደር ሱሌማን ዳውድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአካባቢያችን ሰላም ለማስጠበቅ ባደረግናቸው ጥረቶች የእርሻ ስራችን በተገቢው መንገድ ለማከናወን አስችሎናል።
በአሁኑ ወቅትም በ10 ሄክታር መሬታቸውን በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች ለመሸፈን የዘር ስራ መጀመራቸውን ነው የገለጹት።
አርሶ አደር ደጀኔ አሰፋ በበኩላቸው፣ ዞኑ ለግብርና ልማት ያለው ፀጋ ለወጭ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት ለማምረት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
በዘንድሮው ክረምትም ባለኝ 20 ሔክታር መሬት ላይ ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎችን በመዝራት እስከ 200 ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሰራሁ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የተፈጠረው ሰላም አርሶ አደሩ፣ ባለሃብቱና የጉልበት ሰራተኛው ተረጋግቶ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ቃሲም እንድሪስ ናቸው።
ያላቸውን 65 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አንዳርጌ ጌጡ እንደገለጹት፤ ማሕበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ ከአመራሩ እና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም አስተማማኝ ሰላም እየተፈጠረ በመምጣቱ በዘመናዊ ትራክተሮችና ሜካናይዜሽን ታግዞ የግብርና ስራን ለማቀላጠፍ እንተቻለ ነው የተናገሩት።
በተገኘው ሰላም ለአርሶ አደሩና ባለሃብቱ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በወቅቱ ለማቅረብም እንደተቻለ ነው ያመለከቱት።
በዘንድሮው የመኸር እርሻ 529 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ከ450 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር ተሽፍኗል ብለዋል።
የዞኑ ህብረተሰብም ሰላም የሁሉም መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ያረጋገጠውን ሰላም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።