ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

ደሴ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በመኸር እርሻ ከ60 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ተገኝ አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በ2018/19 የምርት ዘመን ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም በመኸር እርሻ 231 ሺህ 566 ሄክታር መሬት በማልማት ከሰባት ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

የዝናቡ ወቅት ቀድሞ በጀመረባቸው አካባቢዎች እስካሁን ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን ማሳ በዘር መሸፈኑንም ነው ያመለከቱት።

አርሶ አደሩ የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጅዎችን እንዲጠቀም በማድረግ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ከ160 ሺህ ኩንታል በላይ ዘመናዊ ማዳበሪያ መሰራጨቱን ነው የገለጹት።

የዝናብ መዘግየት ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ የመስኖ አማራጭን በመጠቀም የመኸር ሰብል ልማቱን እንዲያከናውኑ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው የመኸር ምርት ዘመን ከለማው 231ሺህ ሄክታር መሬት አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም