ወጣቶች ዓመቱን ሙሉ በሚያከናውኗቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ዓመቱን ሙሉ በሚያከናውኗቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ ወጣቶች በክረምትና በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የወጣቶች ክንፍ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ አባተ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማስመልከት የደም-ልገሳ መርሐግብር አከናውነዋል፡፡
አባላቱ ይህንን አርዓያነት ያለው ተግባር በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ወጣቶች ክንፍ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ አባተ እንደገለጹት፤ ወጣቶቹ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ የልማትና የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚሁ መሠረት የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ አካል የሆነ የደም ልገሳ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት የተከናወነ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶች ደም በመለገስ አርዓያነታቸውን ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቶቹ በማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳትፏቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ለሀገራዊ አብሮነትና ለዜግነት ግዴታ መወጣት ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ፣ ተሳትፏቸውን በቀጣይም በላቀ ሁኔታ እንደሚያጠናክሩት አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ አባላት፣ በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ለመቀነስ ትኩረት አድርገው በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለት በተከናወነው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ላይ የተሳተፉ ወጣቶች እንደገለጹት፤ ደም መለገስ የሰው ልጅን ሕይወት የመታደግ አርዓያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት ወጣቶች መካካል ብርቱካን ገብሬ እንዳለችው ደም መለገስ መስጠት ከባድ ኃላፊነትና ሰብአዊ ግዴታ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ወጣት ጉዲና ስሜ ደም መለገስ የዘወትር ተግባሩ እንደሆነ ገልጾ፣ ደም ከመለገስ ባለፈም በሌሎች የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በደም ልገሳ መርሐ ግብር ላይ ለሰባተኛ ጊዜ መሳተፏን የገለጸችው አዲስ ሙሉጌታ በበኩሏ በጎ ፈቃደኝነት የህሊና እረፍት የሚሰጥ ተግባር መሆኑን ጠቅሳለች፡፡
ወጣቶች እያከናወኑት የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የዜግነት ግዴታቸውን ከመወጣት ባሻገር ለማኅበረሰቡ ደኅንነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።