ቀጥታ፡

በወጪ ንግድ የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ በምርት ጥራትና እሴት መጨመር ላይ ትኩረት ተደርጓል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ):- በሀገሪቱ በወጪ ንግድ የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ በምርት ጥራትና እሴት መጨመር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን የሥራ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን፣ በፓርኩ የአቮካዶ፣ ዘይትና ቡናን የሚያቀናብሩ ኩባንያዎችን ተመልክተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ መንግሥት የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ በእሴት መጨመር ሥራ ላይ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ ያለውን አቅም በአግባቡ በመጠቀምና ገበያው በሚፈልገው መልኩ እሴት ጨምሮ መላክ ላይ የተጀመሩ ጥረቶች የሚጠናከሩ ናቸው ብለዋል።

በፓርኩም በአቮካዶና በቡና ዘርፍ በመሰማራት እሴት በመጨመር የወጪ ገቢ ግኝትና ተኪ ምርት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ተግባሩን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት ከወጪ ንግድ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ በፓርኩ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን ማሳደግ ይገባልም ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ተኪ ምርቶች ላይ እንደሀገር እየተገኘ ያለውን ውጤት ለማጠናከር የሚደረጉ ጥረቶች አበረታች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ሂደት ደግሞ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች መቋቋማቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ቡናን በማቀነባበር ስራ ላይ የተሰማራው የ“መይ መይ ቡና ፕሮሰሲንግ” ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጄይ ሰን፣ በመንግሥት በተደረገላቸው ድጋፍ ታግዘው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም