አስተዳደሩ በአዲሱ በጀት ዓመት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
አስተዳደሩ በአዲሱ በጀት ዓመት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ይሰጣል
ደብረብርሃን፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በአዲሱ በጀት ዓመት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት እንደሚሰጥ አስታወቀ።
የደብረ ብርሃን ከተማ ስፖርት ምክር ቤት የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ የሚመክር ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የስፖርት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ በድሉ ውብሸት በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ከተማዋ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመት ተመራጭ እየሆነችና እያደገች ትገኛለች።
በአዲሱ በጀት ዓመትም ይሕንኑ እድገት በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል ስድስት ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
ስፖርት ወጣቶችን በስብዕና ለመገንባት፣ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚያግዝ በመሆኑ ባለሃብቱና ማሕበረሰቡ በመሰረተ ልማት ግንባታው በንቃት እንዲሳተፍ ነው የጠየቁት።
የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ተክለዮሃንስ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የስፖርት ዘርፉን በመደገፍ ብቁና ተወዳዳሪ ሰፖርተኞችን ለማፍራት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ በ2019 በጀት ዓመት ለሚካሄዱ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎች ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ማጽደቁን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ 12 ካርታና ፕላን ያላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መኖራቸውም ነው የተገለፀው።