ቀጥታ፡

በክልሉ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅንጅት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅንጅት በተሠራው ሥራ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ።

ክልል አቀፍ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ምክክር ፎረም በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የክልሉን ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር፣ የዜጎችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም መሠረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መንግሥት ለቀረጻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስኬት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም ድርጅቶቹ በተለይ በውኃ፣ በሳኒቴሽንና ሃይጂን፤ በጤና እና በግብርና፣ በኑሮ ማሻሻያ እና በትምህርት እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሌሎች ማኅበራዊ ዘርፎች ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ቅንጅታዊ አሠራሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

የቢሮው ምክትልና የፊሲካል ፖሊሲ ትብብር ዘርፍ ኃላፊ ታምራት ታንጋ በበኩላቸው፤ የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን አጋርነትና ትብብር ለማጠናከር ነው ብለዋል።

የሁለቱ አካላት ጥምረት የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያሳድግ በመሆኑ በመካከላቸው ያለው ጥብቅ ትብብር ለክልሉ ዕድገትና ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የክልሉ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር ማሞ ሙልሶ፣ የክልሉን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም