ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በማዕድን ዘርፍ በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል

ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የማዕድን ሃብትን በጥናት በመለየት በተካሄደ የማልማት ተግባር ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የማዕድን ዘርፉ ተኪ ምርትና የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ አይተኬ ኢኮኖሚያዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።

በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናው አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን ሀብት በጥናትና ምርምር በመለየት ወደ ልማት እንዲገባ እየተደረገ ይገኛል።

በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማዕድን ዘርፉ በክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ የተፈጥሮ ጸጋን ለመለየት በተደረገው ሳይንሳዊ ጥናት በርካታ የማዕድን ሀብት በዓይነትም ሆነ በብዛት መኖሩ ተረጋግጧል ብለዋል።

በተለይም የወርቅና የግራናይት ማዕድናትን ጨምሮ የድንጋይ ከሰል፣ ኦፓል፣ ብረትና መሰል ማዕድናት በበቂ መጠን እንዳሉ በማረጋገጥ ወደ ልማት እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የማዕድን ዘርፉ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃት ባሻገር፣ ከ73 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አብራርተዋል።

ዘርፉን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠልም ለ198 ባለሀብቶች አዳዲስ የምርመራና የምርት ፈቃዶች ተሰጥተዋል።

እንዲሁም ለ2 ሺህ 835 ኢንተርፕራይዞች የባህላዊ እና ለ354 አነስተኛ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች የማምረቻ ፈቃድ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በማዕድን ዘርፉ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም የ25 ዓመት የልማትና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ወደ ትግበራ መግባቱን አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም