ቀጥታ፡

ምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው አጀንዳዎች አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል የሚወስኑ ናቸው

ቦንጋ ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦በምክክር ኮሚሽኑ የተለዩት አጀንዳዎች አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል የሚወስኑ መሆናቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ለዓመታት ሲከናወን የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ታሪካዊ ጉባኤ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚጀመረው በዚህ ወሳኝ ጉባኤ ላይ ለመመካከር ከመላው ሀገሪቱ የተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ከሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደውን ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት አስመልክቶ ለተመካካሪዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ የቅድመ ምክክር ማብራሪያና ገለፃ አድርጓል።

በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ በኮሚሽኑ የተለዩት አጀንዳዎች አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል የሚወስኑ ናቸው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መምህር ፍቅረየሱስ ሀብተጊዮርጊስ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ ጉባኤው በሚመች መልኩ አደራጅቶ ያቀረባቸው ስምንቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች እጅግ አስፈላጊና መሠረታዊ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

እነዚህ አጀንዳዎች ላለመግባባት መንስኤ በመሆን ልዩነትን ሲፈጥሩ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት፣ ሀገራዊ መግባባትንና አንድነትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ወንድሙ ካኪሎ በበኩላቸው፤ አጀንዳዎቹ አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ እሳቤዎችን የሚያጎለብቱ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል። 

አጀንዳዎቹ የግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍን የሚከፍቱ መሆናቸውንም አክለዋል።

ለሀገራዊ ጉባኤው የቀረቡ አጀንዳዎች ስር ሰደው የቆዩ ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያስችሉና ሲያጋጥሙ ለነበሩ ችግሮች ውይይትን አማራጭ በማድረግ መፍትሄ ለመሻት አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አዳሙ እሼቱ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም