ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ለሀገራዊ መግባባት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ሀገራዊ መግባባት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡  

ለዓመታት ሲከናወን የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ታሪካዊ ጉባኤ ሊጀመር ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚጀመረው በዚህ ወሳኝ ጉባኤ ላይ ለመመካከር ከመላው ሀገሪቱ የተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡  

ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት ከሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደውን ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት አስመልክቶ ለተመካካሪዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ የቅድመ ምክክር ማብራሪያና ገለፃ አድርጓል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሀገር ሰላምና አንድነትን ያጸናል።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ወደ ተግባራዊ ውይይት ለመግባት መወሰኗ ትልቅ እርምጃ ነው።

ይህ አካሄድ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ከወረዳ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት ስምንት ወሳኝና አንኳር አጀንዳዎችን መለየቱ ለምክክሩ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ጠቁመዋል።

እነዚህ የተመረጡ አጀንዳዎች ኢትዮጵያውያን በቀጣይ  ሀገረ መንግስት ግንባታና ልማት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸውም አክለዋል።

የምክክር ሂደቱ በሕግና በአዋጅ በተቋቋመ ኮሚሽን የሚመራና ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ በመሆኑ፤ አፍሪካና የተቀረው ዓለም ተሞክሮ ሊወስድበት የሚችል አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ምሁሩ ገልጸዋል፡፡ 

ይህ ስልጡን አካሄድ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ በዓለም መድረክ የሚያሳዩበት እንደሚሆንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና አመራር ትምህርት ክፍል መምህር ኡጁሉ ኡኮክ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

ምክክሩ ዜጎች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር አለመግባባቶች እንዲቀረፉና በጋራ ልማት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ዕድል እንደሚፈጥርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የልማታዊ ተግባቦትና የሚዲያ ጥናት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዘለቀ ተሾመ (ዶ/ር)፤ ሀገራዊ ምክክሩ አንድነቷ የተጠናከረና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚጣል ታሪካዊ መሠረት መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ስኬታማነትም እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል የበኩሉን ንቁ ተሳትፎና ጥረት ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም