ቀጥታ፡

በክልሉ የግብርና ሥራን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ሥራን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በወላይታ ዞን ዱጉና ፋንጎ ወረዳ ከ21 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን የብላቴ ኤታ መስኖ አውታር ለአገልግሎት አብቅቷል።


 

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር እንደገለጹት፤ በክልሉ የመስኖ አውታሮችን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

ይህም አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ በማምረት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ ይገኛል ብለዋል።


 

ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክትም ከ1 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከ1 ሺህ 200 በላይ አርሶ አደሮችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ኃላፊው አብራርተዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች ያሉትን የውኃ አማራጮች በመጠቀም በመስኖ እንዲያለሙ በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሥራው አርሶ አደሩን ከተረጂነት በማላቀቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

የዱጉና ፋንጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘካሪያስ ዎንታሞ በበኩላቸው፤ በወረዳው ሰፊ ሊለማ የሚችል የእርሻ መሬት መኖሩን ጠቅሰው፣ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማልማት ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ እየተሸጋገሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዛሬ የተመረቀው የመስኖ ፕሮጀክትም የሦስት ቀበሌ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የብላቴ ኤታ እና የፓንጎ ቢጆ ቀበሌ አርሶ አደሮች፤ ቀደም ሲል የዝናብ ወቅትን ብቻ በመጠበቅ በዓመት አንድ ጊዜ ያመርቱ እንደነበርና ኑሯቸውም ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህ በኋላ በመስኖው በመታገዝ ሰብል እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም