ቀጥታ፡

በምዕራብ እና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች የሚገኙ ፓርኮችን የቱሪዝም መዳረሻነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች የሚገኙ ሦስት ፓርኮችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የሐረርጌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፋኪያ ጀማል ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከተቋቋሙት አዳዲስ ፓርኮች ሁለቱ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን፣ አንዱ ደግሞ በምስራቅ ሐረርጌ የሚገኝ ነው።


 

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ገመቺስ እና አንጫር ወረዳዎች የተቋቋሙት የባሬሞ እና የድንድን ፓርኮች የደን ይዘት እና የዱር እንስሳት መጠን ለማሳደግ የተፈጥሮ ዛፍ ችግኞችን በብዛት የመትከል፣ ደኑን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ ወቅትም የፓርኮቹ የደን መጠን እያደገ በመምጣቱም እንደ አጋዘን፣ ከርከሮ፣ ድኩላ፣ ጉሬዛና ሌሎች የዱር እንስሳት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በደኖቹ ውስጥ ከሚገኙ እንደ አጋዘን ካሉ እንስሳት ሕጋዊ አደን ገቢ እየተገኘ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህም የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ከእንስሳት አደን ከተገኘው ገቢ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው በደን እንክብካቤ ለተሰማሩ የአካባቢው አርሶ አደሮች መሰጠቱን አብራርተዋል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ የተቋቋመው የደባል ሞቲ ጋራ ፓርክ በታሪካዊ ስፍራነቱና በተራራማ አቀማመጡ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በጽሕፈት ቤቱ የፓርኮች እና ኢኮ ቱሪዝም ባለሙያ አቶ ጀቤሳ ፊጡማ በበኩላቸው፣ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የኩርፋ ጨሌ፣ ቀርሳ፣ ገረዋ እና በደኖ ወረዳዎችን የሚያዋስነው የደባል ሞቲ ጋራ ፓርክን በስፋት በማስተዋወቅና በማልማት የቱሪዝም መስህብነቱን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።


 

ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን በተጨማሪም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና ሐረሪ ክልል ጋር በመሆን በተለያዩ ዘዴዎች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከባሕር ጠለል በላይ 3 ሺህ 440 ሜትር ከፍታ ያለው ደባል ሞቲ ጋራ በተፈጥሯዊ አቀማመጡ የጎብኚዎችን ዓይን የሚስብ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ፓርኩን ለሀገር ውስጥና ውጭ ጎብኚዎች ምቹ ለማድረግና የአገልግሎት መስጫ ሎጆችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የሐረርጌ ቅርንጫፍ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ፓርኮች፣ የኢኮ ቱሪዝምና የተለያዩ መስህቦችን ያካተተ ከ77 ሺህ ሄክታር በላይ የደን ክልል ያስተዳድራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም