ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ እና የስነ-ምህዳር መታደስ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አከባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለዘላቂ አካባቢ ጥበቃና ለስነ-ምህዳር መታደስ ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ  (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገበረች ይገኛል።

በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ እስከ አሁን ባሉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ የደን፣ የፍራፍሬና የጥላ ችግኞችን ማልማት ተችሏል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ ተገብቷል።


 

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አካባቢን ከብክለትና ከዕፅዋት መራቆት የምንጠብቅበት፣ እንዲሁም የተዛባውን የተፈጥሮ ሚዛን የምናስተካክልበት ዋነኛና ውጤታማ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።

በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማገገም፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል እና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጠራቀም በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃና ለሥነ-ምህዳር መታደስ የጎላ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህም ባሻገር ዘላቂ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የአየር ብክለትን ለመቀነስና ለቀጣዩ ትውልድ ምቹና አረንጓዴ ሀገርን ለማስረከብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ይህም ለሀገር ውስጥ የአየር ንብረት መረጋጋት ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጥበቃም ጭምር ትልቅ በረከት መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሠራሽ ደን ሥራ አስፈጻሚ አበሩ ጠና በበኩላቸው፤ ከመርሀ ግብሩ ጅምር ጀምሮ የተተከሉት ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የፍራፍሬና ሌሎች ምግብ ነክ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ከማጠናከር ባለፈ ለውጭ ገበያ ቀርበው የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትንና የሥራ ዕድል ፈጠራን እየደገፉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

መርሀ ግብሩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ያላትን ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ እያጠናከረ ሲሆን ለካርቦን ገበያ ተጠቃሚነትም ምቹ መሠረት እየፈጠረ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

የጉለሌ እፅዋት ማዕከል የምርምርና ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደበላ ብሩ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በተለይ ሀገር በቀል ዕፅዋትን በማስፋፋት የሥነ-ምህዳር ሚዛንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሀገር በቀል ዕፅዋት ከአካባቢው የአፈርና የአየር ንብረት ጋር ተስማሚ በመሆናቸው በቀላሉ የሚለሙ መሆናቸውን አንስተው፤ የመሬት ለምነትን፣ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችትንና የአፈር ጥበቃን በማጠናከር የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም