ኢዜአ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያለውን ተግባራዊ ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያለውን ተግባራዊ ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሕብረተሰቡን ከማንቃት ባለፈ በተግባር በመሳተፍ ግንባር ቀደም ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራሮችና ሰራተኞች "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በእንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለአረንጓዴ ዐሻራ ልዩ ትኩረት ሰጥታ የችግኝ ተከላን ባህል አድርጋዋለች።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እያስመዘገበች ያለውን ስኬት ለማስቀጠል እንዲሁም ለዓለም ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የምትጫወተውን ሚና ለዓለም በማሳወቅ በኩል ኢዜአ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ሀገር ያስቀመጠችውን ግብ እንዲሳካ ኢዜአ ማኅበረሰቡን ከማንቃትና መረጃ ከማስተላለፍ ባሻገር፣ በግንባር ቀደምነት በተግባር የመሳተፍ ሚናውን እንደሚያጠናክርም አስታውቀዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ማዕከል እንድትሆን የሚከናወኑ ተግባራትን በማስተዋወቅና ግንዛቤ በመፍጠር በኩል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ የኢዜአ አመራሮችና ሠራተኞች በበኩላቸው፣ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ ዐሻራቸውን በማኖራቸው መደሰታቸውን ጠቅሰዋል።
በኢዜአ የይዘት ፕሮግራም ዳይሬክተር ራሄል አበበ፣ መርሐ ግብሩ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከመጨመር ባለፈ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ እንድትታወቅ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የነጋሪ መጽሄት ምክትል ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ በበኩላቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መረጃ ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን በተግባር በመሳተፍ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ለፍሬያማነታቸው መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የውጭ ቋንቋ ዴስክ ከፍተኛ አዘጋጅ ሄኖክ ታደለ በሰጠው አስተያየት፣ ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን ለማሳደግ የምትሠራው ሥራ ለዓለም ሀገራት አርዓያ እየሆነ መሆኑን ጠቁሟል።
ሌሎች የኢዜአ ባለሙያ የሆኑት ሬድዋን ሸምደስር እና ሰርካለም ዘለቀ በበኩላቸው፣ የለመለመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዐሻራቸውን በማሳረፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።