ቀጥታ፡

የህፃናት መብትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ  ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ  

ሀረር፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የህፃናት መብትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ። 

‘የተጠበቁ ህጻናት  ለበለፀገ ትውልድ’’ በሚል መሪ ሃሳብ  የአፍሪካ ህፃናት ቀን ማጠቃለያ ፕሮግራም በሐረር ከተማ ተካሂዷል።


 

በስነ ስርአቱ ላይ  የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣የሐረሪ  ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ ሚኒስትር ዴዔታዎች፣ የህጻናት ፓርላማ አፈ ጉባዔዎች፣ ታዳጊ ህፃናትና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት አስፈላጊው መሰረተ ልማቶች የማሟላት ስራ እየተከናወነ ነው።


 

በተለይም ውብ፣ ምቹና ጽዱ የመዝናኛ እንዲሁም  የህጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላትንና  የመጫወቻ ስፍራዎች የመገንባትና የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ፣ በተለያዩ ዘርፎች ተሷትፏቸውን የማጎልበት እንዲሁም በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጎጂ እንዳይሆኑ የመጠበቅ፣ ከጥቃት የመከላከልና ሌሎች በርካታ ስራዎችም ስለመከናወናቸው አመልክተዋል።

ከማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህፃናትን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ተጠናክረው  እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ።

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር በበኩላቸው፤ በክልሉ በከተማም ሆነ በገጠር ያሉ ህጻናት መብት፣  ደህንነትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።


 

የህጻናት ሁለንተናዊ እድገት ስኬታማ የሚሆነው በመንግስት ጥረት ብቻ አለመሆኑን ጠቁመው በክልሉ በገጠርና በከተማ ያሉ ህጻናት እኩል ተጠቃሚና ተደራሽነትን ለማጎልበት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ማጎልበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሀገሪቱ የህጻናትን መብት በማስከበር ረገድ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የሀገር አቀፍ የህጻናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባዔ ህፃን ብሌን ድልአርጋቸው ናት።


 

የህጻናትን መብትና ደህንነት የማስጠበቅና ተጠቃሚነትን ከማጎልበት አንጻር መንግስትና ባለድርሻ አካላት እያከናወኑ የሚገኘው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም