የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለልማትና ማህበራዊ አገልግሎት የላቀ ሚናውን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለልማትና ማህበራዊ አገልግሎት የላቀ ሚናውን እየተወጣ ነው
ባህርዳር ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለልማትና ማህበራዊ አገልግሎት የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራቸውን በጥበበ ግዮን ህክምና እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ አኑረዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር)፤ የአረንጓዴ አሻራ ኢንሸቲቭ እንደ ሀገር ለውጥና ስኬት እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጥበበ ግዮን ህክምና እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ችግኞችን በመትከል ጀምረዋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በስሩ በሚገኙ ዘጠኝ ካምፓሶች ችግኞችን በመትከል ፅዱ፣ ውብና ምቹ የመማሪያ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የድርሻውን እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
እንዲሁም ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለልማትና ማህበራዊ አገልግሎት የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
በእለቱ አሻራቸውን ካኖሩት መካከል በዩኒቨርሲቲው የምድረ ግቢ ውበት ዳይሬክተር አማረ ቢተው(ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው ዓመትም 15 ሺህ 200 ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉንና ለዚህም 37 ሄክታር የመካነ እፅዋት መሬት መዘጋጀቱን ጠቁመው ስራው በዛሬው እለት የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረትም ዩኒቨርሲቲው 54 ሄክታር መሬት በአረንጓዴ ልማት መሸፈኑን አስረድተዋል።
በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ሰራተኞች ተሳትፈዋል።