ቀጥታ፡

መንግስት ያመቻቸልንን የስራ ዕድል በመጠቀም ባስፋፋነው ስራ ሌሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት ያመቻቸላቸውን የስራ ዕድል በመጠቀም ባስፋፉት ስራ ሌሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን በሲዳማ ክልል ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ በተፈጠረው ምቹ የሥራ ዕድል ተጠቅመው በርካቶችን ወደ መቅጠር የደረሱ ስራ ፈጣሪዎች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ በቀጣይም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ወጣቶቹ እንደገለፁት፤ መንግስት ባመቻቸላቸው የብድርና የመስሪያ ቦታ በመጠቀም ስራቸውን በማስፋፋት ለሌሎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል። 

በክልሉ በአለታ ወንዶ ከተማ የ”ጊዮን ሻማ አምራቾች ማህበር” አባል ወጣት ኤደን ማቲዎስ እንደገለጸችው፤ በተሰጣቸው አጭር የሥራ ፈጠራ ስልጠና፣ መነሻ ብድር፣ የባንክ ብድር አቅርቦት እንዲሁም የመስሪያና መሸጫ ቦታ ታግዘው አምስት ሆነው ወደ ሻማ ማምረት ሥራ መግባታቸውን ገልጻለች። 

ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመት የሆነው ማህበሩ ስኬታማ በመሆን ከመንግሥት የወሰዱትን 150 ሺህ ብር ብድር መመለሱንና ለ10 ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር አሁን ላይ አጠቃላይ ሀብታቸው ወደ አንድ ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግራለች። 

ከተስፋ መቁረጥ ሕይወት ወጥተው ዛሬ ላይ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰብንና ሌሎችን ወደ መቅጠር መድረሳቸውን ገልጻ፤ ወጣቶች የመንግሥትን ድጋፍ እንደ መነሻ በመጠቀም በትጋት በመስራት መለወጥ እንደሚችሉ አመልክታለች።


 

ሌላው በጩኮ ከተማ በአገልግሎት ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ መሆናቸውን የተናገረው የ”እያየን ካፌና ጌም ዞን ማህበር” ሰብሳቢ ወጣት ሳሙኤል ተስፋ፤ መንግሥት ባመቻቸላቸው የ200 ሺህ ብር ብድርና የመስሪያ ቦታ ታግዘው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግሯል። 

ሥራቸው በአጭር ጊዜ ውጤታማ በመሆኑ በሕይወታቸው ለውጥ ማየታቸውንና ለ32 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሶ፣ አሁን ላይ አጠቃላይ ሀብታቸው ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ነው የገለጸው።

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ባለው የ4ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በአረንጓዴ ልማት ተደራጅተው እንዲሰማሩ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት ግዛው ግርማ ነው።

በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየደገፉ ሲሆን፤ አሁን ላይ ወጣቱን በልማት በማሳተፍ በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት እያደረገ ባለው ጥረት መደሰቱንም ተናግሯል።

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ፤ በክልሉ በከተማና በገጠር ያሉትን አማራጮችና ጸጋዎችን በተቀናጀ መንገድ በመጠቀም፣ የወጣቱን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማጠናከር የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ ናቸው ብለዋል። 


 

በተለይ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ዕድሎችን በማስፋት ረገድ መንግሥት የሰጠው ትኩረት ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም