ቀጥታ፡

በዞኑ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ስፍራዎች እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጓል

ጅማ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦በጅማ ዞን የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ስፍራዎች እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

የጅማ ቴክኒክና ሙያ ክላስተር በ23 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሲያሰለጥናቸው የቆዩትን 2 ሺህ 35 ሰልጣኝ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር እንደገለጹት፤ የበለጸጉ ሀገራት ለስኬት ሊበቁ የቻሉት በቴክኖሎጂ መስፋፋት እና ጥራቱን በጠበቀ የትምህርት አሰጣጥ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ነው።


 

በዞኑም ቴክኖሎጂን ለማስፋፋትና ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ዕቅዱን ከግብ የሚያደርስ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ስፍራዎች እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ዞኑ በርካታ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ያሉት በመሆኑ ዛሬ የተመረቁ ወጣቶች ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ከስራ ጠባቂነት ተላቅቀው የስራ ዕድል ፈጥረው ለብዙ ወጣቶች መትረፍ እንዳለባቸውም አክለዋል።

የጅማ ዞን የስራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የዚያድ አባገሮ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎቹ ባገኙት ሙያና በቀሰሙት ልምድ ከራሳቸው አልፈው ለዜጎች ስራ መፍጠር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።


 

የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ስፍራዎች በመሆናቸው፣ ተመራቂዎቹ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር ማዋል አለባቸው ብለዋል።

ከጅማ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አራት ነጥብ ውጤት በማምጣት የተመረቀው ይሳኮር ብርሃኑ፣ በተማረበት መስክ ስራ ለመፍጠር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።


 

የተለያዩ ሀገራት በቴክኖሎጂ የደረሱበትን ሁኔታ ዘወትር እንደሚከታተል የተናገረው ወጣቱ፣ ሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቴክኖሎጂ ጉዞዋ እያደገ በመሆኑ በዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

በተመሳሳይ አራት ነጥብ ያመጣው ሌላኛው ተመራቂ ደጀን ገብሬ፤ በተማረው የሙያ መስክ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰፊ የስራ እድልን በመፍጠር ከራሱ አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ አቅዷል።


 

ሌላኛዋ ተመራቂ ቤተልሔም በየነ፤ የትምህርት ቆይታዋ ስኬታማ እንዲሆን መምህራኖቿ እና ቤተሰቦቿ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉላት እንደነበር ገልጻለች።


 

አክላም፣ በቀጣይ ባገኘችው ዕውቀትና ልምድ ራሷንና ቤተሰቧን ለመለወጥ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም