ቀጥታ፡

በትምህርት ዘርፍ ብቁ፣ ተወዳዳሪና በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ በትምህርት ዘርፍ ብቁ፣ ተወዳዳሪና በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ የትምህርት ዘርፍን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የትምህርት መሠረትን ከታች ጀምሮ ለማጠናከር በትኩረት መሠራቱን ጠቁመው፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ 35 ሺህ የሚሆኑ ቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

ይህ የመዋዕለ ሕፃናት ግንባታ ቁጥር እጅግ ከፍተኛና ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ዘርፎች የተከናወኑ እነዚህ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ደረጃ በደረጃ በማሻሻል በኩል ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ትምህርት ትውልድ የሚቀረጽበትና ሀገር ወደ ብልጽግና ጉዞ የምትሻገርበት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዚህም የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወኑ የሚገኙ በርካታ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።

የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ በርካታ የቅድመ-መደበኛ፣ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት "ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው ንቅናቄ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ በመሰራቱ ትልቅ ውጤት እንደተመዘገበበት አረጋግጠዋል።

በዚህ ንቅናቄ አማካኝነት ከ17 ሺህ በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፣ ከ39 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ዕድሳት ተደርጎላቸው የውስጥ ግብዓት እንዲሟላላቸው መደረጉን አስታውቀዋል።


 

መንግሥት የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ እንዲቻል ከመሠረቱ መጀመር አለበት በሚል ለቅድመ-መደበኛ ትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የቅድመ-አንደኛ ትምህርት ቤቶች በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠርም ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ መደረጉን አመልክተዋል።

ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሰው ኃይልን ማጠናከርና የመምህራንን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ አንጻር ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ113 ሺህ በላይ መምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በክልሎች ከቅድመ-አንደኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ባሉ የትምህርት እርከኖች ላይ መምህራንን የማብቃትና አቅምን የመገንባቱ ሥራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

በሥነ-ምግባር የታነጹ፣ ሥራ ፈጣሪና ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት በትምህርት ዘርፉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም