የአርባ ምንጭን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አቅሞች በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያስደንቁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአርባ ምንጭን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አቅሞች በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያስደንቁ ናቸው
አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የአርባ ምንጭን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አቅሞች በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያስደንቁ መሆናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው በመገኘት የገጠር ኮሪደርን ጨምሮ በከተማዋ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በቆይታቸው የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በአርባ ምንጭ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ከሀገርም ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የሚጠቅሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በከተሞችም ይሁን በገጠር ዜጎችን የሚጠቅሙና ሀገርን የሚለውጡ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አንስተው ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ስኬት የመንግስት ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።
በአርባ ምንጭ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀከቶችን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የአርባ ምንጭን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አቅሞች በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያስደንቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተዘራ ቀፃዮ፤ በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብተውና ተጠናቀው ለአገለግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች የመንግስትን የልማት ትጋት በተግባር የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ድንበሯ ቱሉ፤ አርባ ምንጭ ከተማ ከተቆረቆረች ረጂም ዓመታት ቢሆናትም ልማት እና እድገቷ እምብዛም እንደነበር አንስተዋል።
በቅርቡ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ግን እስካሁን ለምን መስራት አልተቻለም የሚል ቁጭት የሚፈጥሩ ስለመሆናቸው ተናግረው በዚህ ረገድ መንግስት እያደረገ ላለው ጥረት አመስግነዋል።
በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተገነቡ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን ዕድገት ከማፋጠን ባለፈ ለጉብኝትም ይሁን ኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጋት ነው ብለዋል።
የከተማዋ ዕድገትና የሚታየው ለውጥ ለእንግዶች ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎችም አስደናቂ መሆኑን ተናግረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
አቶ ግርማ ጉንሤ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ እና ጽዱ ከማድረግ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እያሳለጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ባላት ፀጋ ልክ እንድታድግ እያስቻላት ነው ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) ናቸው።
ሰው ተኮር እሳቤ ያለው የለውጡ መንግስት ከተሞችን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የሰነቀው ራዕይ የአርባ ምንጭ ከተማ ፀጋዎች ተገልጠው ወደ ሀብትነት እንዲቀየሩ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገነባ ያለው ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት አብዛኛው እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።