ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋትና በዘርፉ የሴቶችን አመራርነት ለማሳደግ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋትና የሴቶች አመራር ውክልናን በማሳደግ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የባንኩ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሁሉም ባንኮች ያለውን የሴቶች የፋይናንስ አካታችነት በየጊዜው መሻሻሉን መከታተል የሚያስችለውን ሁለተኛውን የሴቶች የፋይናንስ አካታችነት ስኮርካርድ ይፋ አድርጓል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኢኒሼቲቭ የሆነው የኢትዮጵያ ሴት የፋይናንስ ባለሙያዎች ኔትወርክ- (NEWFin) በአመራርና በመሠረታዊ የፋይናንስ ትምህርት የሰለጠኑ አንድ ሺህ ወጣት ሴት የፋይናንስ ባለሙያዎችን አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሁለተኛው የሴቶች የፋይናንስ አካታችነት ስኮርካርድ ግምገማ 32 የሚሆኑ ባንኮች ማለፋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የሴቶች የፋይናንስ ተጠቃሚነት ከባለፈው ዓመት መሻሻል ማሳየቱን አንስተው፣ አሁንም ይበልጥ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በቀጣይም የብድር መጠን ክፍፍልን ማሳደግና የስራ ፈጠራን ማቀላጠፍ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የዘምዘም ባንክ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የኒውፊን (NEWFin) ሊቀ-መንበር መሊካ በድሪ በበኩላቸው፤ ዛሬ የተመረቁት አንድ ሺህ ወጣት ሴት የፋይናንስ ባለሙያዎች የነገ የፋይናንስ ዘዋሪዎችና አመራሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አካታች የሆነ የፋይናንስ ስርዓት ለመፍጠር ያለንን ቁርጠኝነት በማጠናከር የበለጸገች ሀገር ለመገንባት በጋራ እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም