የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን የመደጋገፍ እሴት ከፍ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን የመደጋገፍ እሴት ከፍ የሚያደርግ ነው
ሰቆጣ ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድነት፣የትብብርና የመደጋገፍ እሴትን ከፍ ለማድረግ እያስቻለ መሆኑን በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የ2018 የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ በሰቆጣ ከተማ በዛሬው እለት ተጀምሯል።
የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ትበርህ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ችግሮች በተደራጀ መልኩ በመፍታት የመደጋገፍ ባሕልን ለማሳደግ እያስቻለ ነው።
በአስተዳደሩ በክረምቱ ወቅት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 197 ሺህ በላይ ዜጎችን በማሳተፍ 584 ሺህ 860 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች በአዲስ የመገንባትና የመጠገን፣ ችግኝ የመትከል፣ ደም የመለገስ ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና በሌሎች 17 የስራ ዘርፎች እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድነትና የትብብር እሴትን ይበልጥ በሚያጎለብት መልኩ ለማካሄድ በተሻለ መልኩ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ በበኩላቸው፤ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ እየተካሔዱ ባሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ስኬት እየተመዘገበበት ነው ብለዋል።
በዚህም ወጣቶችን በማስተባበር፣ በመደገፍና በማበረታታት ጥራት ያለውና ችግር ፈች የሆነ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ጥላሁን አበበ ፤ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በየዓመቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ወገኖቹን እያገለገለ እንደሚገኝ ነው የተናገረው።
በዘንድሮ ክረምትም የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን የጀመሩትን ስራ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች የልማት ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል፡፡
የመኖሪያ ቤታቸው የተጠገነላቸው ወይዘሮ ሙሉ አያሌው በበኩላቸው ፤ የተደረገልኝ የበጎ ፈቃድ ስራ ክረምቱን ያለ ስጋት ለማሳለፍ የሚያስችለኝ ነው በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።