ቀጥታ፡

ግብርን በወቅቱ በመክፈል የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የበኩላችንን እየተወጣን ነው

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል በአካባቢው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ ግብር ከፋዮች ገለፁ።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት በ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱንም አስታውቋል።

የከተማዋ ግብር ከፋዮች እንደገለፁት፤ ግብርን በወቅቱ መክፈል ለልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በማግኘት ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላል።

በከተማው የአራዳ ቀበሌ ነዋሪና የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋይ አቶ ፀጋዬ በላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል በአካባቢው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። 

በከተማው የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪዋና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋይ ሐኒያ ኤልያስ በበኩሏ፤ የከተማውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግራለች። 

የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ግብርን በወቅቱ መክፈል የልማት ጥያቄን ለመመለስና ከራስ ለራስ ልማት የሚውል በመሆኑ፣ የዜግነት ግዴታዋን መወጣት ስለመቻሏም ገልጻለች።

በከተማው የሕዝብን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ መክፈል አለበት ያሉት ደግሞ የደረጃ "ለ" ግብር ከፋይ የሆኑት አቶ ኤፍሬም አበራ ናቸው። 

ግብርን በወቅቱ መክፈል በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጎችን ለማፍራት የሚረዱ የትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋት፣ ጽዱ፣ ውብና ማራኪ አካባቢን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ያለው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አውላቸው ዮሐንስ እንደገለፁት፤ በከተማው የገቢ አማራጭን በማስፋት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። 

ጽሕፈት ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ከ2 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በ2019 በጀት ዓመት ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም