ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ግንባር ቀደም ማሳያ ነው ሲሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለፁ።

ዓለምን እየፈተኑ ከሚገኙ ተፈጥሯዊ አደጋዎች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ይህንን ተጽዕኖ ለመከላከልም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጨባጭ ለውጥ እያስገኘ ዘንድሮ ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል።

በእነዚህ ዓመታት በተከናወኑ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች የሃገሪቱ የደን ሽፋን እንዲጨምርና ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አርአያነት ያለው ተግባር የፈጸመች ሲሆን በዘንድሮው ዓመትም ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሐሳብ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እያከናወነችው ያለው ተግባር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትልቅ አርአያ የሚሆን እጅግ አስደናቂ ስኬት መሆኑን አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲና የችግኝ ተከላ ሂደት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ጉዳይ መላውን ዓለም የሚያሳስብ ዓለም አቀፋዊ ክስተት በመሆኑ ኢትዮጵያ ይህንን ሂደት በተለይም ከአፍሪካ አህጉር በግንባር ቀደምትነት እየመራችው እንደምትገኝ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ኒርማላ ፓራናቪታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን የአረንጓዴ ልማት መርሐግብር መተግበሯ እጅግ ብልህነት የተሞላበት አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አበርክቶ ያለው መሆኑን በመግለጽ፣ ስሪላንካ በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ያላትን ፍላጎት ተግባራዊ የምታደርግበትን መንገድ እያጠናች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፓኪስታን የንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ተወካይ ባሲት ሳሊም ሻህ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለኢትዮጵያ የተለየ ውበትና መስህብ ከመለገሱም በላይ፣ ከአየር ብክለት የጸዳ አካባቢን ለማስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዚህ ከፍተኛ ደረጃ መብቃት መቻላቸው ሊደነቅ የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም