የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት የሚያስችሉና የገበያ ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት የሚያስችሉና የገበያ ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት የሚያስችሉና የገበያ ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን የሚገመግም የሴክተር ጉባኤ በሀዋሳ ያካሄደ ሲሆን፣ በቀጣይ በጀት ዓመት የትኩረት ነጥቦች ላይም ውይይት ተደርጓል።
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት የንግድ ዘርፉን በማዘመን በኩል የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጊዜንና ጉልበትን የሚቆጥቡ የዲጂታል አማራጮችን የማስፋት ሥራ በትኩረት መሰራቱንና አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው የተገኙ መልካም ውጤቶች እንዲሰፉ ይደረጋል ብለዋል።
የሸማቹንና ሻጩን በቀጥታ በማገናኘት ገበያን በማረጋጋት በኩል ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን የማጠናከርና ደረጃቸውን የማሻሻል ሥራም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የግብይት ማዕከላትን የማስፋት፣ የምርት ጥራትና ዋጋን ማዕከል ያደረገ የገበያ ቁጥጥር በአዲሱ በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል መሆኑንም አንስተዋል።
በተጨማሪም የኑሮ ውድነትንና ገበያን ማረጋጋት የሚያስችሉ፣ የገበያ ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአፋር ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመድ አብዱልቃድር በክልሉ የገበያ ተደራሽነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ደረጃቸውን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ በንግድ ዘርፉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው።
በክልሉ ከ190 በላይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መገንባታቸውን አንስተው በተያዘው በጀት ዓመት ይህንን የማስፋት ሥራ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።