ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት በማስጠበቅና ቀጠናዊ ትስስሩን በማፋጠን በኩል ለሌሎች አርዓያ እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት በማስጠበቅና ቀጠናዊ ትስስሩን በማፋጠን በኩል ለሌሎች አርዓያ እየሆነ ነው
ደሴ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዲፕሎማሲው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት በማስጠበቅና ቀጠናዊ ትስስሩን በማፋጠን በኩል ለሌሎች አርዓያ እየሆነ መምጣቱን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ካሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ብልሃትና ጥበብ የተሞላበት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አካሄድ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
በተለይም በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በትብብር መስራት ላይ ጸንቶ የዘለቀው ዲፕሎማሲው የዓለምን ቀልብ የሳበና ተቀባይነት ያገኘ ነው ብለዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት በማስጠበቅና ቀጠናዊ ትስስሩን በማፋጠን በኩል አርዓያነት ያለው ተግባር በመሆኑ፣ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሞዴል መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር በር ጥያቄን የመሰሉ ወቅታዊ አጀንዳዎችን በማንሳት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና በትብብር ለመስራት መጠቀም ላይ የታየው ለውጥም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤናና በሌሎችም መስኮች የተመዘገበው እድገትና ለውጥ የኢትዮጵያን ተፈላጊነት በማሳደግ ለዲፕሎማሲው ስኬት መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተፈጠረውን ውጥረት ከማርገብ ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጋሻው መሀመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያስመዘገበችው ድል ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
በተለይ የሰጥቶ መቀበል መርህን አህጉራዊ የጋራ አጀንዳዎች ለማድረግ የተደረገው ጥረት የበለጠ ትኩረት የሳበና የኢትዮጵያን አቃፊነት ለዓለም ያስረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ ከበርካታ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ያጎለበተ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይ ከኢትዮጵያ አልፎ አህጉራዊና ቀጠናዊ አጀንዳዎች ላይ ማተኮሯ ታላቅነቷን ያረጋገጠና የቀድሞ ገናና ታሪኳን የሚመልስ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ ምሁራን ባለን እውቀት የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡