የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን የመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ማህበራዊ ትስስርን የመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ባለፈ በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር የመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ፣ የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ-ደካሞችን ከመደገፍ ባለፈ፣ በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር የመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በመግለጫቸው አብራርተዋል።
በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 14 የተለያዩ በጎ ፈቃድ ተግባሮች ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋናነት የአቅመ ደካማና የእጅ አጠር ወገኖችን ቤት የመጠገን፣ የማደስና አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ስራዎችን ያካትታል ብለዋል።
እንዲሁም ሀገር በቀልና የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃና በእርሻ ሥራዎችን በትኩረት እንደሚከናወኑ ነው የተናገሩት።
በተጨማሪ በሕዝብ አቅም እና አጋር አካል በማስተባበር፣ አዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እና የነባር መማሪያ ክፍሎች እድሳት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና የማዕድ ማጋራትን ጨምሮ ነጻ የምርመራ፣ የሕክምና አገልግሎት እንዲሁም የደም ልገሳ መርሐ-ግብር እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ከተማን ምቹ እና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆን የሚያስችሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር ከ344 ሺህ 614 የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።