የህገ ወጡን የህወሃት ቡድን ግፍና በደል ሸሽተው ከቀያቸው የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች ምን ይላሉ? - ኢዜአ አማርኛ
የህገ ወጡን የህወሃት ቡድን ግፍና በደል ሸሽተው ከቀያቸው የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች ምን ይላሉ?
ሰቆጣ፤ ሐምሌ 4/2018(ኢዜአ)፦ የህገ ወጡን የህወሃት ቡድን ግፍና በደል ሸሽተው ከቀያቸው የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች ምን ይላሉ?
በትግራይ ክልል ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ ከሚገኙት የክልሉ ተወላጆች መካከል ጉዲፋይ አበራ፣ ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን በየእለቱ የሚፈጽማችው ግፍና በደል እየተባባሰ መጥቶ የክፋትን ጥግ አልፏል ይላሉ።
በገጠርም ይሁን በከተማ ሰርተን እንዳንበላ እና ወጥተን እንዳንገባ አፈናውና ዘረፋው እጅጉን የበረታ ሆኖብናል ነው የሚሉት።
በክልሉ ከህፃን እስከ አዋቂ በግዳጅ ለውጊያ እያፈሰ መሆኑን አንስተው ህዝቡ በስጋትና በጭንቀት ውስጥ እየኖረ ነው ብለዋል።
በተለይም ልጆቻችን በዚህ ኋላ ቀር ቡድን የእሳት እራት እንዳይሆኑብን ቀያችንን በመልቀቅ ወደ ሰቆጣ መጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ አጋጣሚውን ያገኙ ሁሉ የህገ-ወጡን የህወሃት ቡድን ግፍና በደል ሸሽተው ወደ አጎራባች ክልሎች፣ ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ውጭ ሀገራት ጭምር እየተሰደዱ ያሉ በርካቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለክልሉ ቀውስ ከህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን በተጨማሪ የሻእቢያ መንግስት ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን አንስተው ህዝቡ መፍትሄ ይሻል ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የክልሉ ተወላጅ ሙላት አወቀ እና የማነ ንጉስ የህገ-ወጡን የህወሃት አፈና በመሸሽ የራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ህይወት ለመታደግ ወደ ሰቆጣ እንደመጡ ይናገራሉ።
ከወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚጥረው ይህ ቡድን የትግራይን ህዝብ መደበቂያና ማምለጫ አድርጎ ጥፋቱን ቀጥሏል ሲሉም ተናግረዋል።
የትግራይ እናቶች በልጆቻቸው ላይ እየተፈጸመ ባለው አፈና፣ ግፍና በደል ሀዘን ላይ መሆናቸውን አንስተው ሕዝቡ የሚታደገው ይፈልጋል ብለዋል።
የትግራይ ክልል ህዝብ ሰላምና ልማት አጥብቆ የሚሻ መሆኑን ገልጸው በግፈኛ የጥፋት ቡድን ታፍኖ መያዙ አሳዛኝ ነው ይላሉ።