ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር ግንባታ የሚቀመጥ ጠንካራ መሠረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር ግንባታ የሚቀመጥ ጠንካራ መሠረት ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር ግንባታ የሚቀመጥ ጠንካራ መሠረት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደውን ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት አስመልክቶ ለተመካካሪዎች በዓድዋ ድል መታሰቢያ ማብራሪያና ገለፃ እያደረገ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል፣ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲያሳትፍ የቆየው ይኸው ሃገራዊ የምክክር ሂደት፣ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን መለየቱ ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅትም እነዚህን መሠረታዊ አጀንዳዎች ይዘው በሀገሪቱ የጋራ እጣ ፈንታ ላይ ለመምከር ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ አራት ሺህ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ይህ ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያውያን በእኩልነት ስለ ሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በቀጥታ የሚመካከሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ይህ ጉባኤ ሀገሪቱ ያሏትን ዘመናዊና ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዲሁም ጠንካራ የውይይት እሴቶችን አቀናጅቶ የሚመራ ልዩ መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የጋራ የነፃነትና የክብር አሻራ መሆኑን አስታውሰዋል።
ትላንት አባቶቻችን ያለ ምንም ልዩነት በአንድነት ቆመው ወራሪውን ጠላት ድል ያደረጉበትና በመላው ዓለም የነፃነት ተምሳሌት የሆነ ታሪክ የፃፉበት ዓድዋ ዛሬም ለእኛ ትልቅ ማስተማሪያ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ዓድዋ እና ሀገራዊ ምክክሩ በነፃነት፣ በእኩልነትና በአንድነት መርህ ላይ አንድ መሆናቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
በእኛ ዘመን ለሀገር ግንባታ የምናስቀምጠው ይኸው ጠንካራ የምክክር መሠረት፣ በቀጣይም በልጆቻችን ዘንድ እንደ ትልቅ ታሪካዊ ድል የሚወሳ ይሆናል ሲሉም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያውያን የጋራ የነፃነትና የክብር አሻራ የሆነው የዓድዋ ድል፣ አሁን ለተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በትልቅ መማሪያነት ሊያገለግል እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡