ቀጥታ፡

በቡና ልማት ላይ የተደረገልን ሙያዊ ድጋፍ ተጠቃሚ አድርጎናል -አርሶ አደሮች

ነቀምቴ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ዓመታት የቡና ልማትን ለማሳደግ የሚደረገው ድጋፍና ሙያዊ እገዛ ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በዞኑ የጉቶ ጊዳ ወረዳ አርሶ አደር ሀብታሙ ፍቃዱ፤ "ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለቡና ምርት በተሰጠው ትኩረትና የሚደረገውን ሙያዊ ድጋፍን በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት ጀምረናል፤ በዚህም ይበልጥ ተጠቃሚ እየሆንን ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የቡና ምርት ልማትና ጥራት በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማቅረብ በገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን በማልማት ስራቸውን ይበልጥ ለማሻሻል ማቀዳቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የቢሎ ቦሼ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ደረጄ አርፍሳ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ያረጁ የቡና ተክሎችን በመንቀል እና በመጎምደል እንዲሁም አዳዲስ ምርጥ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን እየተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በጥራት መጓደል ምክንያት በሚያመርቱት ልክ ለገበያ ማቅረብ እንዳልቻሉ ያስታወሱት አቶ ደረጄ፣ አሁን ላይ ግን ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የቡናና አትክልት ልማት ቡድን መሪ አቶ አስፋው መኮንን በበኩላቸው፤ በዞኑ በየደረጃው በተሰጠ ስልጠና እና በተደረገ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ፣ ጥራቱን የጠበቀ ቡና እየተመረተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

አርሶ አደሮች ከተከላ እስከ ምርት አሰባሰብ ያለውን የጥራት አጠባበቅ ሂደት እንዲረዱ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአመራረት ስልትን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።

ከ96 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና ተነቅሎ በአዲስ ችግኝ የተተካ ሲሆን፣ 320 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና ደግሞ መጎንደሉን ተናግረዋል።

ዘንድሮም በመንግስትና በግል የቡና ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ከ300 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የተከላ ስራውም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም