ቀጥታ፡

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰባዊ እሴቶችን በማጎልበት ለበጎ ዓላማ መተባበርን ያጠናክራል

ሐዋሳ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ማህበረሰባዊ እሴቶችን በማጎልበት ለበጎ ዓላማ እርስ በርስ መተባበርን እንደሚያጠናክር ተሳታፊ ወጣቶች ገለጹ። 

መርሃ ግብሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች እውቀትና ባህላቸውን እንዲለዋወጡ ከማስቻሉም ባለፈ ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት ትልቅ መድረክ መሆኑም ተመላክቷል።

የዘንድሮ ወሰን ተሸጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀግብር ''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የፌደራልና የሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በሃዋሳ ከተማ ተጀምሯል።


 

መርሃ ግብሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ወሰን ሳይገድባቸው በበጎነት ህዝባቸውን ከማገልግል ባለፈ የባህል እሴቶችና ልምዳቸውን  የሚለዋወጡበትን ምህዳር እየፈጠረ ነው፡፡

ኢዜአ ይህንኑ ተግባር ለማስቀጠል በተያዘው ክረምት  ወደ ሥራ ከገቡ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ጋር ቆይታ  አድርጓል።

ወጣቶቹ እንዳሉት፤ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በርስ የመደጋገፍ ማህበረሰባዊ እሴትን ስለሚያጎለብት ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ነው።

ከወጣቶቹ መካከል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የመጣችው ሳምራዊት አበራ፤የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግስት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል ብላለች። 

እሷም ባለፉት ጊዜያት በተግባሩ በመሳተፍ የህሊና እርካታ ማግኘቷንና ይህን ልምዷን በመያዝ በዘንድሮው ወሰን ተሸጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፏን ተናግራለች፡፡

ፕሮግራሙ ከማህበራዊ  አገልግሎቱ ባለፈ የሌሎች አካባቢዎችን ባህልና የማሕበረሰብ እሴትን ለመረዳት እንዳስቻላትም ገልጻለች፡፡


 

ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመጣው ወጣት ዑስማን ሃሰን በበኩሉ፤ መርሀ ግብሩ የተቸገሩ ወገኖችን የመደገፍ የቆየ ባህልን ለማዳበር የራሱ ድርሻ አለው ብሏል።

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትን የሚያጠናክርና ወጣቶች እውቀትና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ  የሚያግዝ ነው ብሏል፡፡

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  ወጣቶች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያስቻለ ነው ያለችው ደግሞ በሲዳማ ክልል የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ምህረት ፈለቀ ናት፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የትብብርና የአንድነት መንፈስ እሳቤን ወደ ተግባር ይበልጥ ለመለወጥ ተግታ እንደምትሰራም  ተናግራለች፡፡

ከሐረር ከተማ የመጣው ወጣት ሙጀህዲን ረመዳን በበኩሉ፤ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደመር መንግስት የወለደው አዲስ እሳቤ መሆኑን ጠቅሶ የዚህ ትውልድ አካል በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ፕሮግራሙ የወጣቶችን የተደመረ አቅም ለመጠቀም የሚያስችልና የባህል ልውውጥና እና  ትብብርን የሚያጠናክር እንደሆነም አንስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም