ቀጥታ፡

የማስ ስፖርት መጠናከር የዜጎችን የአብሮነት እሴት ያጎለብታል

ሐረር፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የማስ ስፖርት እንቅስቃሴዎች መጠናከር ጤናማ ትውልድ እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ የዜጎችን የአብሮነት እሴት የሚያጎለብት መሆኑን የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ገለጸ።

በሐረር ከተማ በሚገኘው የአባድር ፕላዛ መናፈሻ ስፍራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሄዷል። 


 

ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች፣ የሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች፣ ወጣቶች፣ ህጻናትና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙራድ አብዲ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአካል ጥንካሬ፣ ለአእምሮ እድገት እንዲሁም ጤናማና ብቁ ዜጋን ለማፍራት ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል። 


 

የክልሉ መንግስት 'ስፖርት ለሁሉም፣ በሁሉም ስፍራ' በሚል መርህ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከጤና ጥቅሙ ባለፈ የዜጎችን የአብሮነት እሴት የሚያጎለብትና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመቅረጽ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

መሰል ስፖርታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።

የሐረሪ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ በበኩላቸው፤ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ሰፋፊ የኮሪደር ልማትና የቅርስ ጥበቃ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል ብለዋል። 


 

እነዚህ ስራዎች አደጋ ተደቅኖባቸው የነበሩ ቅርሶችን ለመታደግ ከማስቻላቸው ባለፈ፣ ሐረርን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ይበልጥ ውብ፣ ሳቢና ማራኪ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም፣ በክልሉ መጪው ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም “ሩጫ በህያው ሙዚየም” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ የዛሬው የአካል ብቃት እንቅስቃሴም የዚሁ ትልቅ ስፖርታዊ ክስተት ማሟሟቂያና የስፖርት ቱሪዝምን የማስተዋወቂያ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም