በባሌ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን በማስፋት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን በማስፋት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል
ሮቤ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን በማስፋት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መታየቱን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
በዞኑ በበጀት ዓመቱ ከ89 ሺህ 500 ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተመላክቷል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ ለሚ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን በማስፋት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተገኝተዋል።
በዞኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ89 ሺህ 500 ለሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው በከተማ ግብርና ልማት፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በዶሮና እንስሳት እርባታ ዘርፎች መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከ964 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር የተመቻቸላቸው ሲሆን፣ 4 ሺህ 540 ሄክታር የእርሻ መሬት እንዲያኙ መደረጉን አክለዋል።
ለእነዚሁ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች በተመቻቸው ብድር በመጠቀም 50 የእርሻ ትራክተሮች የተገዙላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
የአጋርፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልቃድር ኡስማን በበኩላቸው፣ በወረዳው የከተማ ግብርናና የጎጆ ኢንዱስትሪ ኢኒሼቲቭ የበርካታ ወጣቶች የገቢ ምንጭ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
በወረዳው በበጀት ዓመቱ በዘርፉ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለሆኑ 10 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ከ185 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በአጋርፋ ወረዳ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች መካከል አደም አብደላ በሰጠው አስተያየት፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ በመሰማራት ውጤታማ በመሆን ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግሯል።
በቀጣይም ወደ ተሻለ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሸጋገር ጠንክሮ እንደሚሠራ ገልጿል።
በከተማው በወተት ላሞች እርባታ በመሰማራት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የተናገረው ደግሞ ወጣት አብዱለጢፍ አብዱልመናን ነው።
በሥራው ውጤታማ በመሆን ቤተሰቡን ከማስተዳደር ባለፈ ጥሪት ማፍራት መጀመሩን ተናግሯል።
በባሌ ዞን ባለፈው የበጀት ዓመት 75 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮ እንደነበር ተጠቅሷል።