አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ ከእንግሊዝ፤ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ ተጠባቂ ፍልሚያዎች - ኢዜአ አማርኛ
አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ ከእንግሊዝ፤ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት የሚደረጉ ተጠባቂ ፍልሚያዎች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የሚገቡ ቀሪ ሁለት ሀገራት የሚለዩባቸው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ከሌሊቱ 10 ሰዓት አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ በካንሳስ ሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርጀንቲና 16 ውስጥ ግብጽን 3 ለ 2 በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች።
የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት አርጀንቲና በጨዋታው እስከ 80ኛው ደቂቃ 2 ለ 0 ብትመራም በ13 ደቂቃዎች ውስጥ ውጤቱን በመቀልበስ አሸንፋለች።
የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በውድድሩ ተሳትፎ ታሪኳ ለ10ኛ ጊዜ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።
ተጋጣሚዋ ስዊዘርላንድ ኮሎምቢያን በመለያ ምት 4 ለ 3 በማሸነፍ ከ72 ዓመታት በኋላ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች።
ጨዋታው በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እና 30 ደቂቃ ግብ አልተቆጠረበትም።
ስዊዘርላንድ ስምንት ውስጥ ስትገባ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።
እ.አ.አ በ2014 በብራዚል በተካሄደው 20ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ 16 ወስጥ ተገናኝተው አርጀንቲና በሊዮኔል ሜሲ ጎል 1 ለ 0 ስዊዘርላንድን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው አልፋለች።
ቡድኖቹ ከ12 ዓመታት በኋላ በመድረኩ በድጋሚ ተገናኝተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በውድድሮች እና የወዳጅነት ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ ተገናኝተው አርጀንቲና አምስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ስዊዘርላንድ እስከ አሁን አርጀንቲናን አሸንፋ አታውቅም።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ 8 ግቦችን ያስቆጠረው የ39 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ሊዮኔል ሜሲ፣ የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል።
ሜሲ በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ 21 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪም ነው።
አርጀንቲናዊው ኮከብ በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓለም ዋንጫው ለስዊዘርላንድ አራት ግቦችን ያስቆጠረው የ29 ዓመቱ ብሬል ኢምቦሎ፣ በዚህ ጨዋታ ላይ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ቁልፍ ተጫዋች ነው።
በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ኖርዌይ ከእንግሊዝ በሚያሚ ስታዲየም ከሌሊቱ ስድስት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ኖርዌይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ብራዚልን 2 1 ለ በመርታት በታሪኳ በዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ አልፋለች።
ተጋጣሚዋ እንግሊዝ ከአዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ሜክሲኮ በተፈተነችበት ጨዋታ 3 ለ 2 በማሸነፍ ስምንት ውስጥ ገብታለች።
ሶስቱ አናብስቶች በዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸው ወደ ሩብ ፍጻሜ ሲያልፉ የአሁኑ ለ10ኛ ጊዜ ነው።
የአውሮፓ ሀገራቱ ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው ተገናኝተው አያውቁም።
በተለያዩ ውድድሮች እና የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ 12 ጊዜ ተገናኝተው እንግሊዝ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ኖርዌይ በሁለት ጨዋታዎች ድል ቀንቷታል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይተዋል።
እንግሊዝ በ12ቱ ጨዋታዎች ላይ 28 ጎሎችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ኖርዌይ ሰባት ግቦችን አስቆጥራለች።
እ.አ.አ በ1937 ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ጨዋታ እንግሊዝ 6 ለ 0 ማሸነፏን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዓለም ዋንጫው ላይ ሰባት ጎሎችን ያስቆጠረው የኖርዌው አርሊንግ ሃላንድ እና ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ያሳረፈው እንግሊዛዊው ሃሪ ኬን በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
የኖርዌው አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ እና የእንግሊዙ ጁድ ቤሊንግሃም መሐል ክፍል ላይ የሚኖራቸው ፉክክርም ትኩረትን ስቧል።
እንግሊዝ የማሸነፊያ የቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች።
ባልተጠበቀ ሁኔታ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው ኖርዌይ፣ ያለ ጫና መጫወቷ አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ልታልፍ የምትችልበትን እድል ይፈጥርላታል።
የዛሬ ጨዋታ አሸናፊዎች በግማሽ ፍጻሜው ይገናኛሉ።