ቀጥታ፡

ስፔን ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ስፔን ቤልጂየምን 2 ለ 1 አሸንፋለች።

ማምሻውን በሎስ አንጀለስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፋቢያን ሩዊዝ ስፔንን መሪ ያደረገችውን  በ30ኛ ደቂቃ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ጎሉ በጥሩ የኳስ ቅብብል የተገኘ ነበር።

ቻርልስ ዲ ኬቴላር በ41ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠረው ጎል ቤልጂየምን አቻ አድርጓል።

ዲ ኬቴላር በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ሶስት አድርሷል።

ተቀይሮ የገባው ሜኬል ሜሪኖ በ88ኛው ደቂቃ የአሸናፊነቷን ጎል ለስፔን አስቆጥሯል።

የ30 ዓመቱ ሜሪኖ 16 ውስጥ ስፔን ፖርቹጋልን ስታሸንፍ ተቀይሮ በመግባት ግብ በማስቆጠር ስፔንን አሸናፊ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ተጫዋቹ ምርጥ ተቀያሪነቱን በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ አሳይቷል።

ስፔን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ አስተናግዳለች።

የ29 ዓመቱ የስፔን ግብ ጠባቂ ኡናይ ሲሞን በዓለም ዋንጫው ከ649 ደቂቃዎች በኋላ ግብ ተቆጥሮበታል።

ሲሞን በውድድሩ ላይ ለረጅም ሰዓታት ግብ   ሳይቆጠርበት የቆየ ግብ ጠባቂ በመሆን አዲስ ክብረ ወሰን ሰብሯል።

ስፔን በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድሎችን በመፍጠር ተሽላ ተገኝታለች።

የቤልጂየም የአጨዋወት ስልት መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ላይ ያተኮረ ነበር።

የአማዱ ኦናና እና ዩሪ ቲሊማንስ በጉዳት ምክንያት አለመሰለፍ የቤልጂየምን የአማካይ ክፍል አሳስቶታል።

የ34 ዓመቱ የቤልጂየም ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮርቶዋ በጉዳት ምክንያት 71ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ስፔን ለግማሽ ፍጻሜ  አልፋለች። ለሶስተኛ ጊዜ አራት ውስጥ ገብታለች።

ስፔን ለዋንጫ ለማለፍ ከፈረንሳይ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ቤልጂየም በዓለም ዋንጫው ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም