በከተማው በአዲሱ በጀት ዓመት 12 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው በአዲሱ በጀት ዓመት 12 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል
ሀዋሳ፤ ሐምሌ3/2018(ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በአዲሱ በጀት ዓመት 12 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በከተማው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት እና የአገልግሎት አቅርቦት ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት መሰጠቱም ተመላክቷል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ መልኩ ማርቆስ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማው ከ7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 102 ፐርሰንት ማሳካት ተችሏል፡፡
በ2019 ግብር ዘመን12 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ገልፀው ከሐምሌ 1 ጀምሮ ገቢ የመሰብሰብ ሥራው መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት የገቢ አሰባሰብ ሥራው በቴክኖሎጂ መታገዙ፣ የባለሙያዎች አቅም መገንባቱና የገቢ ምንጮችን ማስፋት በመቻሉ ገቢን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተያዘው የግብር ዘመንም የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢን የማሳደግ፣ ከቅጥር የሚገኝ ገቢን እና የአከራይ ተከራይ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ መልኩ አስረድተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የገቢ አሰባሰብ ሥርዐት በመዘርጋት በባንክ የክፍያ ማረጋገጫ ብቻ ገቢ እየተሰበሰበ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ዓመት ጀምሮም የባንክ ክፍያን በማስቀረት በቴሌ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግ እና ሌሎች ዘመናዊ የክፍያ አማራጮች ብቻ ገቢን ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገው ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡
በከተማው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት እና የአገልግሎት አቅርቦት ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።
ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የገቢ አሰባሰብ ሂደት ግብር ከፋዮች ግብራቸውን እየከፈሉ እንደሚገኙም አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል በታቦር ክፍለ ከተማ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ መስከረም አስፋው በየዓመቱ ግብራቸውን በወቅቱና በታማኝነት የመክፈል ልምድ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
ከዜጎች የሚሰበሰበው ገቢ በከተማዋ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንደሚውል በመረዳታቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ግብራቸውን በወቅቱ እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡
በግብር ሰብሳቢው አካል የሚሰጠው አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቅልጥፍናው እየጨመረ የመጣ በመሆኑ ያለ እንግልት ግብራቸውን በቀላሉ መክፈል እንደቻሉም ጠቁመዋል፡፡
በሀዋሳ መናኸሪያ ክፍለ ከተማ በእንግዳ ማረፊያ የአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ኢያሱ በገጄ ግብር ለሀገራችን የምንከፍለው የዜግነት ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋ የልማት ሥራ ጥቅሙ ለነዋሪው እንደሆነ ጠቅሰው ልማቱ እንዲፋጠን ግብራቸውን በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡