ቢሮው የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ ችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ ችሏል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በመደገፍና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ መቻሉን አስታወቀ።
ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ያከናወናቸውን ተግባራት፣ የቢሮውን የለውጥ ጉዞና የተገኙ ስኬቶችን የሚያሳይ ኤግዚቢሽንም በዛሬው ዕለት በይፋ ከፍቷል።
የቢሮው የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ቢሮው የግብር ከፋዩን እንግልት ለመቀነስና ግልጽነትን ለመፍጠር በርካታ የሪፎርም ስራዎችን አከናውኗል።
ወደ 24 የሚጠጉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ይህንንም በማሳተም ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ተደራሽ መደረጉንና ከግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መሰራቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በቢሮው ስር ባሉ 17ቱም ቅርንጫፎች የሚገኙ ከሰባት ሺህ በላይ ሰራተኞችን መቆጣጠር የሚያስችል የቴክኖሎጂ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡ እንዴት እየተከናወነ እንደሚገኝ ዋና ቢሮ ሆኖ በቀጥታ መከታተል የሚያስችል የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዘሃራ መሐመድ በበኩላቸው፤ ከቢሮው ጋር እየተደረገ ያለው የተቀናጀ አሰራር አዎንታዊ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በተደረገው የጋራ ጥረትና ቅንጅታዊ አሰራር፣ ከነጋዴው ማህበረሰብ የተነሱ የተለያዩ ቅሬታዎችን በጋራ በመገምገም 620 ለሚሆኑ ነጋዴዎች ለገጠሟቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡