ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና መግባባት የሰፈነባትን ሀገር ለትውልድ ለማሻገር ያስችላል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ለቆዩ ያለመግባባቶች በሰለጠነ መንገድ በመመካከር ሀገራዊ መግባባት በመፍጠር፣ሰላምና ልማት በማስፈን ለትውልድ ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን የሴቶች አደረጃጀት ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፤ የዋናው ጉባኤ ተሳታፊ የሀገር ውስጥና የውጭ የሕዝብ ወኪሎችም አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።

በዋናው የምክክር ጉባኤም የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣የተቋማት ግንባታ፣የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳይ፣ ሙስናና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሰላም ግንባታ የተሰኙ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች የሚመከርባቸው ይሆናል።

የሴት አደረጃጀትና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ችግሮቻችንን በምክክር ከመፍታት ይልቅ የኃይል አማራጭን በመከተል የፖለቲካ ፍላጎትን ለማስፈጸም የሚደረግ ጥረት አዋጭ አይደለም።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ለቆዩ ያለመግባባቶች በሰለጠነ ውይይት በመመካከር ሀገራዊ መግባባትን፣ሰላምና ልማት የሰፈነባትን ሀገር ለትውልድ ለማሸጋገር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የሴቶችን ተሳትፎና አካታችነት የሚያረጋግጥና ሴቶች በዜጎች መካከል ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ከግብ የሚያደርስ ስልጡን መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም እንዳሉት፤ ሴቶች ሀገራዊ መግባባትን በመገንባት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሀገራዊ ጉዳዮችና ጥያቄዎች አሏቸው።

በዚህም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሂደት የነበረውን የሴቶች ንቁ ተሳትፎ በማሳደግ፣በዋናው ጉባኤም በወኪሎች አማካኝነት የሚሳተፉበት ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተካተቱ ዐበይት አጀንዳዎች የሴቶችንና የማህበረሰቡን የዘመናት ጥያቄ በስልጡን የውይይት መድረክ ትኩረት አግኝተው መፍትሔ እንደሚያገኙ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እናትዓለም እንዳለ በበኩላቸው፤ ለዘመናት በቆዩ አለመግባባቶች በሚከሰቱ ግጭቶች ሴቶች ግንባር ቀደም ተጠቂና የጉዳት ሰለባዎች ናቸው ብለዋል።


 

በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰቢያና የተሳታፊ ልየታ ሂደትም ሴቶችን የሚመለከቱ የሕግና ፍትሕ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የፍትሕ ተጠቃሚነትና የፖለቲካ ተሳትፎ አጀንዳዎች ተጠናቅረው መቅረባቸውን አስታውቀዋል።

የሴቶች አጀንዳዎችም በዋናው የምክክር ጉባኤ በተካተቱ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ውስጥ መካተታቸውን አስረድተዋል።

የጉባኤው ተሳታፊ የሕዝብ ወኪሎችም ስልጡን ምክክርን በማስቀደም፣ጠንካራ ሀገረ መንግሥትና ሀገራዊ መግባባትን የሚያመጡ ምክረ ሃሳቦችን በታላቅ ኃላፊነት ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም