በዞኑ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራርን በማረጋገጥ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራርን በማረጋገጥ እያገዘ ነው
መቱ፤ ሐምሌ 3/2018 (ኢዜአ):- የኢሉአባቦር ዞን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራርን በማረጋገጥ የህብረተሰቡን እንግልት እየቀነሰ መሆኑ ተገለጸ።
የኢሉአባቦር ዞን ያዮ ወረዳ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በዛሬው ዕለት ተመርቆ አገልግሎት ጀምሯል።
የኢሉአባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ማህበረሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ታልሞ የተቀረጸ ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዞኑ ወደ ስራ የገቡ ማዕከላትም የህብረተሰቡን የአገልግሎት ተደራሽነት የሚያሰፋ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አሰራርን እያሰፈኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የተገልጋዩን ድካምና እንግልት ማስቀረት እያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በያዮ ወረዳ ስራ የጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 32 የስራ ክፍሎችን በአንድ ላይ ያካተተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይም አሰራሩን በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል ቄስ ሳሙኤል ደምሴና ወይዘሮ ወርቄ ተፈራ፤ ማዕከሉ የተገልጋዩን መጉላላት የሚያስቀርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን የሚያሻሽል በመሆኑ ስራ መጀመሩ አስደስቷቸዋል።
ብልሹ አሰራሮችን በመቀነስ ረገድ መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙት መሰል እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ወይዘሮ ገላኔ ኮርሳና አቶ ጀማል ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ህዝቡን ከምልልስና ከተጨማሪ ወጪ የሚታደግ መሆኑን አንስተዋል።
የመንግስት አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶችም ከተለመደውና ለቅሬታ ከሚዳርጉ ብልሹ አሰራሮች በመላቀቅ፣ ማህበረሰቡን በታማኝነት የማገልገል ባህላቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።