ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢንቨስትመንት የቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት የዜጎችንና የቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃ ደኅንነት ፎረም ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ስብሰባውን በአዲስ አበባ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል።


 

በመድረኩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ የሳይበር ደኅንነት፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና መሰል ዓለም አቀፍ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ በስፋት ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የደኅንነት ፈተናዎችን በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥና በአጋርነት መርህ ላይ የተመሰረተ በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወነች ነው።

በዚህም ቀጣናዊ ጠንካራ የትብብር ማዕቀፎችን በመዘርጋት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና በሰዎች መነገድ ወንጀልን ለመከላከል እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ፣ የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴ ከማክሸፍ ባሻገርም፣ ልማትን በማፋጠን ድኅነትና ሥራ አጥነትን በጋራ ለመቀነስ አስደናቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የዲጂታል መሠረተ ልማትና ሳይበር ደኅንነት አቅምን በማጎልበት የዜጎችንና ቁልፍ ብሔራዊ ተቋማትን ለመጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም አካታች፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሁም ለሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደርና ለሕግ የበላይነት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም እያጋጠሟት ያሉ ስጋቶች ውስብስብና በፍጥነት የሚቀያየሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግሥታትም የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል የመረጃ ልውውጥና ሕጋዊ ማዕቀፎችን በማጣጣም ትብብራቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና አሜሪካ የጤና ዘርፍ አጋርነት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወኑ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመዋጋትም በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፎረሙ መስራችና ሊቀመንበር ሮበርት ፒተንገር ፤ ፎረሙ ኢትዮጵያ ለልማትና ዴሞክራሲ ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም የመሪዎቿን ርዕይ ለመላው ዓለም ለማሳየት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም