ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ሥራዎች የእሳት አደጋና የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ  የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ሥራዎች የእሳት አደጋና የጎርፍ ተጋላጭነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ ማስቻላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ የተቋማዊ አቅምን በማጠናከርና የአደጋ ስጋት አመራር ሥርዓቱን በማዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን እየሠራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን በመገምገም በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይም ዉይይት አካሂዷል።


 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አሕመድ መሐመድ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ ዋነኛ መሣሪያ ሆኗል።

የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ሥራዎች በመከናወናቸው መሰረታዊ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመው፤ በተለይ ቀደም ሲል ለጎርፍ፣ ለእሳት አደጋና ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎችን ደኅንነታቸው መጠበቁን ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም ለተለያዩ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች፣ የሙያ ምክር አገልግሎት፣ የቴክኒክ ድጋፍ እና የደህንነት መስፈርት ፍተሻዎችን በማከናወን በተቋማት ውስጥ የአደጋ መከላከል ባህል እንዲጠናከር ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ 

ኮሚሽኑም በቀጣይ የአደጋ መከላከል፣ የምላሽ አቅም ማጠናከር፣ ዲጂታል አሠራርን ማስፋፋት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ለተሻለ የአገልግሎት ውጤት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡


 

በአራዳ ቅርንጫፍ የኮሚሽኑ ባለሙያ የሆኑት ትዕግስት ተክለአብ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ከማኅበረሰቡ ጋር በመደራጀት በብሎክና በወረዳ ደረጃ የቅድመ አደጋ መከላከል ሥራዎች ተከናውነው ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል።

ሌላው የኮሚሽኑ የአደጋ መከላከል ባለሙያ ማስረሻ ጥላሁን በበኩላቸው፣ አደጋዎች ሲከሰቱ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት በፍጥነት በመድረስ አደጋዎችን የመቆጣጠር ሥራ በውጤታማነት መከናወኑን ገልጸዋል።


 

የኮሪደር ልማቱም ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎችን በማልማት የኮሚሽኑን የአደጋ ቅነሳ ሥራ እንዳገዘ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በተፈጥሯዊና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ላይ የመከላከልና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በስፋት መከናወናቸው ተጠቁሟል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም