ቀጥታ፡

በዞኑ አቮካዶን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል

ደብረ ማርቆስ፤ ሃምሌ 3/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን  አቮካዶን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ ገለጹ።

ዋና አስተዳዳሪው እንደገለጹት ፤በዞኑ ደብረ ኤልያስ ወረዳ አቮካዶን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ ነው።

ለዚህም የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን፣ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡና በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸውን የአቮካዶ ችግኞችን በማዘጋጀት የችግኝ ተከላ ስራ ተጀምሯል ነው ያሉት።

ዞኑ በሰብል ልማት ትርፍ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች  አንዱ በመሆኑ አርሶ አደሩን በብዝሃ የአመራረት ስልት በማሳተፍ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ በበኩላቸው ፤በተያዘው ክረምት በደብረ ኤልያስ፣ ጎዛምንና ማቻከል ወረዳዎች የፍራፍሬ ልማትን በኩታ ገጠም የማካሄድ ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

በዛሬው እለትም በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በአበሸም ቀበሌ አቮካዶን በኩታ ገጠም ለማልማት የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር መካሔዱን አስረድተዋል።

በእለቱም በወረዳው ብቻ በ100 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም አቮካዶ ለማልማት የሚያስችል የችግኝ ተከላ መካሄዱን አብራርተዋል። 

በአጠቃላይ በዞኑ በኩታ ገጠም ለማልማት የሚያስችል ከ 917 ሺህ በላይ የአቮካዶ ችግኝ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን በክረምቱ ከ 2 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በላይ ፍራፍሬን በኩታ ገጠም ለማልማት የሚያስችል ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም