በጎንደር ከተማ ወደ 49 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ወደ 49 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሯል
ጎንደር፤ ሃምሌ 3/2018 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 49 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ የስራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ሥራና ክህሎት መምሪያ ያለፈውን በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሄዷል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በከተማዋ በተካሄዱ የኢንዱስትሪ፣ የከተማ ግብርና፣ የንግድና አገልግሎት ዘርፎች ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት ተሰርቷል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ለ44 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በተደረገ ጥረት፣ ከ48 ሺህ 900 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከዕቅድ በላይ መፈጸም መቻሉን ገልፀዋል።
ከዕቅድ በላይ ማስመዝገብ የተቻለውም በተገኘው ሰላም ባለሀብቱ ተረጋግቶ ወደ ልማት በመግባቱና አመራሩና ባለሙያው የተጠናከረ ድጋፍ በማድረጋቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበርም ለ2 ሺህ 689 ኢንተርፕራይዞች 665 ሚሊዮን ብር ብድር በማሰራጨት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የሥራ ዕድሉን መፍጠር የተቻለውም በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በአነስተኛ ንግድና ሌሎች የሥራ ዘርፎች መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም መምሪያው ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጎን ለጎንም ለ856 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በማድረግ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማደረጉን ገልጸዋል።
ከጎንደር ከተማ አስተዳደር መሬት መምሪያ ጋር በመተባበር በኮሪደር ልማት ለተነሱ 334 ግለሰቦች የመስሪያና የመሸጫ አገልግሎት መስጫ ሼድ በማስገንባት ማስረከብ መቻሉንም አክለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ግርማይ ልጅዓለም በበኩላቸው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሥራ ዕድል ፈጠራ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ይህም የከተማው አስተዳደር የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ስራን በዋነኝነት ይዞ በየጊዜው እየገመገመና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ በመስራቱ የመጣ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።