የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተወሰደው አማራጭ ገበያን የማስፋት ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተወሰደው አማራጭ ገበያን የማስፋት ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2018(ኢዜአ)፦የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተወሰደው አማራጭ ገበያን የማስፋት ሥራ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት የኑሮ ውድነትንና ገበያን ለማረጋጋት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
ከተወሰዱ ቀዳሚ እርምጃዎች መካከል የሸማቾችን አማራጭ ማሳደግ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ተደራሽነት ከ2 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ለዚህም በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ህገወጥ ተግባራትን መከላከልና መቆጣጠር፣ የምርት አቅርቦትን ማሳደግና አማራጭ ገበያን ማስፋት ላይ ትኩረት መደረጉን ነው ያብራሩት።
በተለይም በንግድ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የህገወጥ አካላትንና የደላሎችን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትን በማደራጀት ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን ለመፍጠር በተደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ 804 አዳዲስ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መከፈታቸውን ጠቅሰው፥ በአጠቃላይ 2 ሺህ 369 መድረሳቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ማዕከላት ያለምንም የደላላ ጣልቃ ገብነት ቀጥተኛ ሸመታ የሚከናወንባቸው በመሆናቸው በተለይ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በእጅጉ መደገፍ መቻላቸውን ነው ያነሱት።
ከዋጋ አኳያም ከመደበኛው ገበያ ጋር ሲነጻጸር ከ15 በመቶ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ያላቸው መሆኑ ተናግረዋል።
በማዕከላቱ በኩል በግብርና እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ሰፊ የገበያ ትስስር የተፈጠረ ሲሆን በዚህም በስፋት አትክልትና ፍራፍሬ፣ የሰብል ምርቶች እና የኢንዱስትሪ ምርቶች እየቀረቡ ነው ብለዋል።
እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተጨማሪ የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማዘመን የሁለተኛ ደረጃ የገበያ ማዕከላትን የመገንባት ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
ይህንን ዘመናዊ አሠራር በስፋት በመተግበር ረገድ አዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆናቸውን በመጥቀስ፥ ወደ ሌሎች ክልሎችም ተሞክሮው እየተስፋፋ ነው ብለዋል።
እነዚህ ሁለተኛ ደረጃ የግብይት ማዕከላት የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ለገበያ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል።